ቅዱስ ጊዮርጊስ የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጨዋቾችን እንዳያስፈርም የታገደበት ውሳኔ በፊፋ የጸና መሆኑን ክለቡ ገለፀ !

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2017 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ላስፈረማቸው አራት የውጪ ተጨዋቾች ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ ምክንያት ተጨዋቾቹ በመክሰሳቸው ፊፋ ለሁለት የዝውውር ወቅቶች ተጨዋቾችን እንዳያስፈርም  እገዳ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን ክለቡ በተሰጠው 30 ቀን ውስጥ እዳውን መክፈል ባለመቻሉና ይግባኝም ባለመጠየቁ እገዳው የጸና ሆኗል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአቶ ጀማል አህመድ በስጦታ ያገኘውን ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ለአራቱም ተጨዋቾች ከነቅጣቱ መክፈል ችሏል።

ፈረሰኞቹ የቅጣት ክፍያውን ከነ ወለዱ ሲከፍልም ፊፋ በእያንዳንዱ አራት ተጨዋቾች ተቀጥቶ የነበረው የዝውውር እገዳ እንደተነሳ  የሚገልፁ አራት ደብዳቤዎችን ክለቡ ከፊፋ ተቀብሏል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ የያዝነውን የውድድር ዘመን በተሻለ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ሊረዱት የሚችሉ አራት የውጪ ሀገር  ተጨዋቾችን ለማስፈረም ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣቱ የሚታወስ ሲሆን ክለቡ እነዚህን ተጨዋቾች ሲመለምልም እዚህ መጥተው መፈረም የሚችሉ መሆን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማረጋገጫ ተሰጥቶ ተጨዋቾቹ የህክምና ምርመራ አጠናቅቀው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቲ ኤም ኤስ ለመመዝገብ ሲሞከር እገዳው እንዳልተነሳለት ታውቋል፡፡

በመሆኑም ቅዱስ ጊዮርጊስ በአራት ተጨዋቾች ክስ የተጣለበትን ቅጣት ሙሉ በሙሉ ከፍሎ መጨረሱን የሚገልፅ ደብዳቤ ማግኘቱንና እግዱ ግን አለመነሳቱን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የተጨዋቾቹ ጠበቃ ጭምር ቢፅፉም በተደጋጋሚ ከፊፋ ያገኘነው ህዳር 11 ቀን 2018 ዓ.ም በFPSD-20952 መዝገብ ቁጥር በተሰጠው ውሳኔ የፀና መሆኑን የሚገልፅ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ መልዕክቶችን ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አሜሪካ ማያሚ እና ሲዊዘርላንድ ዙሪክ ከተሞች  በመገኘት የዚህን ውሳኔ ማብራሪያ የሚጠይቁ ሁለት የፊፋ ፈቃድና ልምድ ያላቸውን ጠበቆች በመቅጠር ጉዳዩን በአሸናፊነት ለመቋጨት ሁሉንም አማራጮች ክለቡ የተጠቀመ ቢሆንም በፊፋ የተጫዋቾች ሁኔታና ዝውውር ደንብ (RSTP) አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 4 መሰረት ቀሪው የምዝገባ እገዳ ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቅ እንደሚገባና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀገር ውስጥ ተጨዋቾችን ብቻ ማስፈረም እንደሚችል አቋሙን አጽንቷል።

በዚህም መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በቀጣይ ከሚከፈተው የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጨዋቾችን ከማስፈረም የሚታገድ ይሆናል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ደንቦችንና ውሳኔ እንደሚያከብር ገልፆ ጉዳዩንም በሙያዊ እና በኃላፊነት መንፈስ ለመቋጨት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን በክለቡ ይፋዊ ገፅ አስታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *