የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ | የዲስፕሊን ውሳኔዎች!

1. ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል በተደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ መድን ተጫዋቾች በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ውስጥ አምስት (5) ቢጫ ካርድ እና አንድ (1) የረዳት አሰልጣኝ ቢጫ ካርድ በድምሩ ስድስት ቢጫ ካርድ የሚያሰጡ ጥፋቶች ስለመፈጸማቸው ከዕለቱ የጨዋታና የውድድር አመራሮች ሪፖርት ቀርቧል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀጽ 65 በፊደል ተራ ቁጥር ሀ መሰረት ቡድኑ የብር 5,000 (አምስት ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል።

2. ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከቀኑ 9:00 ጀምሮ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል በተደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በ32 ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድን ተጫዋች መለያ ቁጥር 3 ያፌድ ሀይሉ (መታወቂያ ቁጥር 18-500) ተቀይሮ በሚወጣበት ወቅት ከጨዋታው ሜዳው ከወጣ በኋላ ለብሶት የነበረውን መለያ በማውለቅ ንዴትና ብስጭት በተቀላቀለበት ሁኔታ በዋናው አሰልጣኝ አካባቢ ወርውሮ መሬት ላይ በመጣል ሳያነሳ ወደ ተጠባባቂዎች መቀመጫ ወንበር ላይ ሄዶ የተቀመጠ መሆኑና ተወርውሮ የተጣለውን መለያ የኢትዮጵያ መድን ቡድን አመራር ያነሳው ስለመሆኑ የዕለቱ የውድድር አመራር ሪፖርት ቀርቧል።


​የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴው የቀረበውን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ተጫዋቹ የቡድኑ መግለጫ የሆነውን መለያ እና ለዋናው አሰልጣኝ ክብር ባለመስጠት አውልቆ መጣልና መረገጥ አስነዋሪ ድርጊት የፈጸመ መሆኑን በማረጋገጥ ለፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀጽ 66 በፊደል ሐ ተራ ቁጥር 7 መሰረት ብር 10000 (አስር ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኗል።

3. ግንቦት 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከቀኑ 9:00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል የግማሽ ፍጻሜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ በተካሄደበት ወቅት ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን አርማ የያዝና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች ከታች ጋለሪው የነበሩ 20 (ሃያ) መቀመጫዎች በሰባበርና ከቦታቸው ተነቅለው የተጣሉ በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 5 ምዕራፍ 2 አንቀፅ 20 ተራ ቁጥር 14 መሰረት ቡድኑ (ክለቡ) እንዲተካ እና እንዲያሰራ ተወስኗል።

ለመተካት እና ለማሰራት እንዲቻል ባለንብረቱ በሚያቀርበው ግምት መሰረት እንዲከፈልም ተወስኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *