​የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሀገራችን እግር ኳስ ለማሳደግ እያከናወነ ያለው የሚደነቅ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እንደገለጹት፣ የድሬዳዋ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያሳየ ያለው አበረታች እንቅስቃሴ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብሉዋል።

​ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት በትላንትናው ዕለት በድሬዳዋ ድል ላስመዘገበው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቤተ መንግሥት በተዘጋጀው የእራት ግብዣ መርሐ ግብር ላይ ነው።

​አቶ ኢሳይያስ ጅራ በንግግራቸው ወቅት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ካለበት ደረጃ ተላቆ በአህጉር ደረጃ ተፎካካሪ እንዲሆን ለማስቻል በድሬዳዋ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ስራዎች በሁሉም ክልሎች ሊስፋፉ እንደሚገባ ገለፀው፣ ለዚህም የድሬዳዋን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማሰራጨት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

​ይህ በድሬዳዋ እየታየ ያለው የእግር ኳስ መነቃቃትና የፌዴሬሽኑ ድጋፍ፣ በቀጣይ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባትና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሩህ ተስፋን ለመፈንጠቅ ትልቅ መሠረት እንደሚሆን ታምኖበታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *