ጋሞ ጨንቻ ወደ 2019 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ከጫፍ ደርሷል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በጂማ ስታዲየም 4:00 ሰዓት ላይ ጋሞ ጨንቻ 2ለ0 ነቀምቴ ከተማን በማሸነፍ ወደ 2019 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ከጫፍ ደርሷል፡፡

በመጀመሪያ አጋማሽ በጭማሪው ደቂቃ ፎሳ ሳዴቦ በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል 1ለ0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል ያመረ ሲሆን ሁለተኛ አጋማሽ 49ኛ ደቂቃ ማቴዎስ ኤልያስ ባስቆጠረው ጎል አፕሎቹ አሸንፈው መውጣት ችለዋል።
ጋሞ ጨንቻ 17 ጨዋታ አድርጎ 38 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከተከታያቸው የካ ክፍለ ከተማ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነትም ወደ 5 ከፍ ማድረግ ችለዋል ።

ነቀምቴ ከተማ በ2018 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች 7 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ሲለያይ 10 ጨዋታዎችን ሽንፈት አስተናግዶ አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ 7 ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ አንድ ጨዋታ እየቀረው ወደ 2019 የኢትዮጵያ ሊግ አንድ መውረዱን ያረጋገጠ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል።
የካ ክ/ከተማ ከንብ በሚያደርገው ጨዋታ ነጥብ ከጣለ ጋሞ ጨንቻ የመጨረሻውን ከቡራዩ ክ/ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ሳይጠብቅ ወደ 2019 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጉን ያረጋግጣል።
7:30 በተደረገው የ17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ሐረር ከተማ 1ለ0 አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ማሸነፍ ችሏል።

ለሐረር ከተማ የማሸነፊያ ግብ በመጀመሪያ አጋማሽ 34ኛ ደቂቃ አብዱልፈታ መሐዲ ማስቆጠር ችሏል።
ሐረር ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 14 በማድረስ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሽንፈት ያስተናገደው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በ13 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ቡድን ሆኗል።
ቀጣይ ጨዋታ
ሐረር ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና
አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ከ ነቀምቴ ከተማ
10:00 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና 1ለ0 ሻሸመኔ ከተማን አሸንፏል።

የወራጅ ቀጠናው ስጋት እንድሁም ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማደግ ተስፋ የለላቸው ሁለቱ ቡድኖች ደረጃቸውን ለማሻሻል ያደረጉት ጨዋታ 77ኛ ደቂቃ ላይ ታረቀኝ ታደሰ ባስቆጠረው ጎል ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታውን አሸንፎ መውጣት ችሏል።
ቤንች ማጂ ቡና ማሸነፉን ተከትሎ 24 ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሽንፈት ያስተናገደው ሻሸመኔ ከተማ 21 ነጥቦች በመሰብሰብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቀጣይ ጨዋታ
ቤንች ማጂ ቡና ከ ሐረር ከተማ
ሻሸመኔ ከተማ ከ ንብ ክለብ
በዛሬ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በጂማ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታዎችን ተከታትለዋል።

