ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ውድድሮች ስታስጠራ የቆየችው አትሌት የብርጓል መለሰ በዛሬው ዕለት በደረሰባት ድንገተኛ አደጋ በ36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
አትሌቷ ዛሬ ማለዳ በጃን ሜዳ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ልምምድ ላይ ሳለች በድንገት የመውደቅ አደጋ ደርሶባት ወደ ጤና ተቋም ብትወሰድም ሕይወቷን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል።
ሚያዝያ 1982 ዓ.ም የተወለደችው አትሌት የብርጓል መለሰ፤ ከ2003 ዓ.ም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንስታ በበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ስኬታማ ውጤቶችን አስመዝግባለች።
በተለይም በሂዩስተን፣ በፕራግ እና በሻንጋይ ማራቶን በተለያዩ ዓመታት በቀዳሚነት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2018 የሻንጋይ ማራቶንን ስታሸንፍም የስፍራውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ነበር።
በፓሪስ ግማሽ ማራቶን ሁለት ጊዜ፣ በፖርቹጋል ግማሽ ማራቶን ደግሞ አንድ ጊዜ ባለድል ለመሆን የበቃችው የብርጓል፤ በ2015 ኮንጎ ብራዛቪል ላይ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያን ወክላ የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች።
በዚሁ ዓመት በቺካጎ ማራቶን ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በማግኘት በ”ማራቶን ሜጀርስ” ስሟን አስጠርታለች።
