የኢትዮጵያ ከፍተኛ  ሊግ ምድብ ለ 18ኛ ሳምንት መጀመሪያ ቀን ውሎ !

ወደ 2019 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚያልፈውን ቡድን ለመለየት ወሳኝ ምዕራፍ  ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ዛሬ በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም በሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል።

ሀላባ ከተማ 1-2 መንጌ ቤላሻንጉል

የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ 7:30  መሪው ሀላባ ከተማ ሽንፈት ሲያስተናግድ መንጌ ቤላሻንጉል ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ውጤት አስመዝግቧል።

መንጌ ቤላሻንጉል በመጀመሪያ አጋማሽ 6ኛ ደቂቃ የኋላሸት ሰለሞን ከመልስ ውርወራ ያገኘውን ኳስ በግራ መስመር ለአዛሪ ሙሳ የሰጠውን ኳስ አዛሪያ ከሶስት ተጨዋቾ አልፎ ለሲራጅ ከድር ያሻገረው ኳስ ሲራጅ ከድር ጎል አስቆጥሮ መንጌ ቤላሻንጉልን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ሀላባ ከተማ 30ኛ ደቂቃ በሰለሞን ገመቹ የፍፁም ቅጣት ምት ያስገኘውን ኳስ መንጌ ቤላሻንጉሎች በዋና ዳኛ ውሳኔ ደስተኛ ሳይሆኑ ቀርተው 3 ደቂቃዎችን ከተከራከሩ በኋላ በ34ኛ ደቂቃ በዮናታን ኋይሉ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል።

በጨዋታው መንጌ ቤላሻንጉል እግር ኳስ ክለብ ከፍፁም ቅጣት ምት ላይ ባላቸው ቅሬታ የቴክኒክ ክስ አስዘዋል።

ሲራጅ ከድር በሊጉ 7ኛ ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ደረጃ ላይ ከየካ ክፍለ ከተማ ድልነሳው ሽታው እኩል ማድረግ ችሏል።

የመጀመሪያ አጋማሽ በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ወደ መልበሻ ክፍለ ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች በሁለተኛ አጋማሽ ጥሩ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን 74ኛ ደቂቃ ላይ አብርሃም ምህረት ግሩም ግብ ከርቀት በማስቆጠር ዳግም መንጌ ቤላሻንጉልን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በመንጌ ቤላሻንጉል 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ደሴ ከተማ 1-1 ሶሎዳ ዓድዋ

የ18ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ 10:00 ሰዓት 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደሴ ከተማ ከሶሎዳ ዓድዋ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት  አጠናቋል።

የመጀመሪያ አጋማሽ በተቀዛቀዘ መልኩ የተጀመረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል።

ሀላባ ከተማ በመንጌ ቤላሻንጉል ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ደሴ ከተማ ከሀላባ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ብርቱ ጥረት ማድረግ ብችልም 90ኛ ደቂቃ በተቆጠረበት የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጎል በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ደሴ ከተማች ሲሆን በአማኑኤል ግዛቸው አማካኝነት 73ኛ ደቂቃ ከግብ ጠባቂው እንዳሻው እሸቴ ያገኘውን ኳስ ቢላል ገመዳ በጥሩ ሩጫ ከራሱ ሜዳ ክፍል ይዞ በመሄድ በግራ መስመር አንድ ተጨዋች አልፎ ያሻማውን ኳስ በሀዋሳ ግብ ለማስቆጠር ተቸግሮ የነበረው አጥቂው አማኑኤል ግዛቸው በግንባሩ በግሩም ሁኔታ ወደ ጎልነት በመቀየር ደሴ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሶሎዳ ዓድዋ 88ኛ ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተስፋዬ እና አለምሰገድ አድማሱ በጥሩ አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ደሴ ግብ ክልል ሲደርሱ ምስጋና ፈይሳ ጥፋት ሰርቶ የፍፁም ቅጣት ምት ሶሎዳ ዓድዋ ሲያገኝ አሸናፊ ተስፋዬ በአግባቡ ተጠቅሙ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በማስቆጠር ሶሎዳ ዓድዋን አቻ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው ተጨማሪ +6 ደቂቃዎች ከተጨመሩ በኋላ 90+3ኛ ደቂቃ ላይ የሶሎዳ አድዋ ግብ ጠባቂው ለይኩን ነጋሽ በደሴ ከተማ አጥቂው እሱባለው ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ደሴ ከተማዎች ማግኘት ብችሉም የመስመር አጥቂው ቢላል ገመዳ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።

የጨዋታው ድራማዊ ክስተት

የዕለቱ ዋና ዳኛ መለሰ ንጉሴ ቢላል ገመዳ የፍፁም ቅጣት ምቱን ከመምታቱ በፊት የሶሎዳ ዓድዋ ተጨዋች የማነ ገ/ሥላሴ ቀድሞ ፍፁም ቅጣት ምት መምቻ ሜዳ ውስጥ ገብቷል በማለት የፍፁም ቅጣት ምቱ ይደገማል ብልም የዕለቱ ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ማስረሻ ኃይለማርያ እንዳይደገም እና ጨዋታው በመልስ ምት እንድጀምር ለዋና ዳኛ መለሰ ንጉሴ ካስረዱ በኋላ በተነሳው ውዝግብ ጨዋታው 15 ደቂቃ ከተቋረጠ በኋላ በመልስ ምት ልጀመር ችሏል።

122 ደቂቃዎችን የፈጀው ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

✍ በአቤኔዘር መስፍን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *