የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 16ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን 4:00 ላይ ነቀምቴ ከተማን ከ ቡራዩ ክ/ከተማ አገናኝቷል።
ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ሁለትም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበራቸው ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ተስተውለዋል።
በመጀመሪያ አጋማሽ በዋና አሰልጣኝ ቾምቤ ገ/ህይወት የሚመራው ነቀምቴ ከተማ በእስጥፋኖስ ተማም አማካኝነት ሁለት ጊዜ ከረጂም ርቀት ወደ ግብ የተሞከሩ ኳሶችን የቡራዩ ክፍለ ከተማ ግብ ጠባቂ በልስቲ ቀረብኝ ግብ እንዳይሆኑ ማድረግ የቻለ ሲሆን በዋና አሰልጣኝ አይናለም ግርማ (ቦረና) የሚመራው ቡራዩ ክ/ከተማ ከቀኝ መስመር ተስፋሁን ሙሉጌታ የተሻገረውን ኳስ ጴጥሮስ ገዛኸኝ ከነቀምቴ ከተማ ግብ ጠባቂ ማቴዎስ ሰለሞን ጋር ፊትለፊት ተገናኝቶ የሳተው ኳስ ተጠቃሽ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ 66ኛ ደቂቃ ላይ ቡራዩ ክ/ከተማዎች አማካዩ ወጋየሁ ብርሃኑ ለአጥቂው ሊሬ አባይነህ ለማሻገር ሲሞክር የነቀምቴ ከተማ ተከላካዩ ሰጠኝ ኢየሱስ በራሱ ጎል ላይ አስቆጥሮ ጨዋታው በቡራዩ ክ/ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።
7:30 ላይ የካ ክ/ከተማን ከ ቤንች ማጂ ቡና አገናኝቷል።
በዋና አሰልጣኝ ያሬድ ቶለራ (ድሬ) የሚመሩት የካ ክ/ከተማዎች በጨዋታው 24ኛ ደቂቃ ላይ በእዩኤል አበባየሁ ጎል ቀዳሚ መሆን ብችሉም መደበኛው ደቂቃ ልጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ በቀረበት ሰዓት መሐመድ ናስር ለቤንች ማጂ ቡና ጎል አስቆጥሮ ሁለቱ ቡድኖች 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አድርጓል።

ሁለተኛ አጋማሽ 53ኛ ደቂቃ ላይ ፍሬገነት ኤርሚያስ በግንባሩ ያስቆጠረው ጎል ዳግም የካ ክ/ከተማን ወደ መሪነት የመለሰ ኳስ ሲሆን 89ኛ ደቂቃ ከ29 ሜትር ርቀት ላይ የግብ ጠባቂው አብነት ይስሃቅ አቋቋም ተመልክቶ አጥቂው እንዳለ ደባልቄ (ካኪሽ) ከመልስ ውርወራ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የካ ክ/ከተማ ጨዋታውን 3ለ1 አሸፎ እንድወጣ ማድረግ ችሏል።

ተጠባቂው የ16ኛ ሳምንት ጨዋታ ባቱ ከተማን ከንብ (አየር ኋይል) ያደረጉት ጨዋታ በንብ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጋሞ ጨንቻ ከሐረር ከተማ ጋር ያደረገው ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ማጥበብ የሚችልበት አጋጣሚ ባቱ ከተማዎች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

በዋና አሰልጣኝ ኢዮብ ማዓሌ (አሞካቺ ) የሚመራው ንብ ክለብ 20ኛ ደቂቃ ማኑሄ ጌታቸው ያቀበለው ኳስ አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ከ35 ሜት ርቀት አከባቢ አክርሮ በመምታት ባስቆጠረው ግሩም ጎል ጨዋታው 1ለ0 አሸንፏል።
ዋና አሰልጣኝ ራማቶ መሐመድን በቅጣት ምክንያት ያጣው ባቱ ከተማ ተከታታይ ሽንፈት ለማስተናገድ ሲገደድ ንብ ነጥቡን ወደ 26 ከፍ ማድረግ ችሏል።
ባቱ ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ የካ ክ/ከተማ 2ኛ ደረጃን ተረክቧል።

