ሲዳማ ቡና ከ20 ዓመት በታች በተከታታይ ለሁለተኛ ዓመት ለፍፃሜ ያደረሰው አሰልጣኝ አመሃ ዘውዴ ከዳጉ ስፖርት ጋር ቆይታ አድርጓል።
አሰልጣኝ አመሃ ዘውዴ ስለ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ምን ይመስል ነበር?
ትልቅ ስሜት አለው ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከነማ በተስፋ ቡድን ጨዋታ ለዋንጫ ለማለፍ የመጀመሪያው ታሪካዊ ጨዋታ ነውና የዝህ ታሪክ የመጀመሪያው ሰው በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል እጅግ ከባድ ጨዋታ ነበር ግን በእግዚአብሔር እርዳታ ተወጥተነዋል ።
በመጀመሪያ አጋማሽ በልጣችኃል በሁለተኛ አጋማሽ የተበለጣችሁበት ምክንያቱ ምንድነው ?
እውነት ለመናገር በመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ እንደጨረስን ተሰምቶኝ ነበር ሁለተኛ አጋማሽ ምንም የጠበቅኩት ነገር አልሆነም እጅግ በጣም ጥሩ ነበሩ ሀዋሳ ከነማዎች እሱ ብቻ አይደለም ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ቻሉ ከዛ በኃላ ሙሉ ለሙሉ ጨዋታው ከእኛ የወጣ ነበር ፈጣር
ልፋታችንን ቆጠረልንና ሊያልቅ ሲል መሳይ ዮሐንስ ግብ አስቆጥሮ አሸነፍን እንጂ ሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶብን አንዳንዴ ወጣቶች ላይ የሚፈጠር የስሜት መረበሽ አለ እና እነዚህ ነገሮች ዋጋ ሊያስከፍለን ተቃርቦ ነበር ግን ተወጥተነዋል ።
ስለ ጨዋታ አቀራረብ እና ሁለተኛ ጎል ሲቆጠር ስልት እና ስሜታዊ ሊያደርግህ የቻለው ነገር ምንድን ነው በጨዋታው?
በርግጥ እግር ኳስ የስሜት ስፖርት ነው እንደነገርኩህ ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን እነሱ ሙሉ ተቆጣጥረውት ነበር በሰዓት ቆሜ እያሰብኩ የነበረው ማን ማን የመለያ ምቱን ይመታል የሚለውን ሂሳብ እየሰራሁ ነበር እሱን እየቆጠርኩ እያለ ነው ሁለተኛ ጎል ያስቆጠርነው እና በጣም ስሜታዊ ነበርኩኝ ምክንያቱም ለሁለተኛ ጊዜ በሁለት ዓመቴ ነው ተስፋ ላይ ከመጣሁ ሁለቱንም ዓመት ተከታታይ ለፍፃሜ መድረስ ለእኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው ከፕሮጀክት አሰልጣኝነት ተነስተህ ይህንን ማሳካት በጣም ትልቅ ነገር ነውና በዛ ምክንያት በጣም ነው ደስታ የፈጠረብኝ በአጋጣሚ ሌላ ነገር ተባለ እንጂ ደስታ አገላለጽ ነበር በማለት ገልጿል።
የአሰልጣኝነት ፍልስፍና እና የውጤታማነት ምስጥር
በፕሮጀክትም ሳለህ አንተ የምትይዛቸው ቡድኖች ከአንድ እስከ ሶስት ወይም ለዋንጫ ይደርሳሉ ለዚያ ነገር ጥንካሬ ብለህ የምታስባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው ?
በጣም እምነት አለኝ በፈጣሪ ጠንክሬ እንድሰራ አቅሙን ሰጥቶኛል እና ሁልጊዜ ስራዬ ላይ እገኛለሁ አልጎልም ጠንክረህ ከሰራህ ሁሉም ነገር ያንተ ነው እንደዝህ ነው የማምነው ከልጆቼ ጋርም በጣም ቅርብ ነኝ ሩቅ ሆኜ የሚሰራ አሰልጣኝ ስላልሆንኩ ብዙ ነገሮችን ለመለዋወጥ አይከብደኝም ከፕሮጀክት ጀምሮ ሁልጊዜ ውድድር ሲገባ የማስበው ከዋንጫ መብላት በላይ በመዝጊያው ቀን መገኘት እፈልጋለሁ እና በጣም ነው የምወደው የመዝጊያ ቀን የመጀመሪያ ቀን ስለ ማጠቃለያ ውድድር አይደለም የምናስበው ተከታታይ ይህንን ውድድር ያደረገ የለም ተከታታይ እናደርገዋለን ብለን ነው የተነሳነው እና አንድ ጨዋታ ነው የቀረችን እናሳካዋለን ሲል ሀሳቡን ገልጿል።
በሁለተኛ ዙር የውድድር ጊዜ ላይ በተጫዋቾች ጉዳት በኩል ጫና ነበር እና ያንን ነገር እንዴት ልትቋቋመው ቻልክ?
በርግጥ አሁንም በቡድን ውስጥ ጉዳት ፈተና ሆኗል እጅ እና እግር ተሰብሮ ቡድን ላይ መቀጠል በጣም ከባድ ነው ወጣቶች ናቸው ይህንን ውድድር እንኳን ሲንጫወት ተቀያሪ ግብ ጠባቂ የለንም አንድ ግብ ጠባቂ ብቻ ነው ያለን ዓመቱን ሙሉ ስንጫወት ወደ 25 ጨዋታ አድርገናል 25ቱንም ጨዋታ በአጠቃላይ አምስት ተከላካይ ነው ያለን ይሄ ነገር ስሜታዊ ያደረገኝ ጽናት ነው በጣም ብዙ ነገር ችለን ነው እዚህ ላይ የተገኘነው እና በመጨረሻም የልፋታችን ፍሬ እያፈራን ነው ብዬ አስባለሁ በማለት ተናግሯል።
ምን አይነት የጨዋታ ስል ትመርጣለህ?
ፈጣን አጨዋወትን እመርጣለሁ አሁን ላይ እኔ በጣም ኳስ ሲብላላ አልወድም ደጋግመህ በተቃራኒ ግብ ክልል መገኘት አለብህ ከ40 ጎል አልፈናል መሳይ ዮሐንስ ብቻውን 17 ጎል አለው ተከላካዮችም እንኳ 3 ጎል ነው ያላቸው እና በጣም ፈጣን ሽግግር ያለው አጨዋወት ደስ ይለኛል ሲል ተናግሯል
ካለፉት አሰልጣኞች የተገኘ ልምድ
በተጫዋችነትህ ዘመን ያካበትከው ልምድ አሁን ላለው የአሰልጣኝነት ስራህ ምን አስተዋጽኦ አድርጓል?
እኔ በጣም እድለኛ ነኝ በአጋጣሚ ትላልቅ አሰልጣኞች ናቸው ያሰለጠኑኝ በስም ለመጥቀስ ሀዋሳ ከነማ ውስጥ አሁን ዋና ቡድን ላይ ያለው ቅዱሴ ፤ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከነማ ያለው ኤፍሬም ፣ የሀዋሳ ከተማ ዋና ቡድን አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና ነብዩ ጋር ሰርቻለሁ እና እነዚህ በጣም ትላልቅ አሰልጣኞች ናቸው በወቅቱ ጥሩ ተጫዋች ስለነበርኩ የቡድኑ አምበል ስለነበርኩኝ ብዙ ልምድ ከእነሱ አግኝቻለሁ እና የብዙ ሰው ጥርቅም ይመስለኛል አሁን ይህንን ማንነቴን የሰራው ሲል አመሃ ዘውዴ ገልጿል።
የእግር ኳስ ፍልስፍና በአጭሩ እንዴት ትገልፀዋለህ?
ለእኔ እግር ኳስ ማለት «ጎል» ነው መጀመሪያ የማስበው ጎል ካለ እግር ኳስ አለ ጎል ከሌለ እግር ኳስ ተመልካቾችን ማዝናናት አይቻም የእኔ ፍልስፍና በቀላሉ መንገድ ጎል ማስቆጠር ነው በቀላሉ መንገድ ደግሞ ጎል የምታስቆጥረው በፍጥነት ነው እና ለእኔ እግር ኳስ ላይ ፍጥነት መሰረታዊ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው።
ከዚህ ቀደም ካሰለጠንካቸው ቡድኖች ውስጥ ትልቅ ስኬት ያገኘህበት አጋጣሚ እና የተጠቀምክበት መንገድ?
በሲዳማ ቡና የ20 ዓመት የመጀመሪያ ዓመቴ ነበር እና ከውድድሩ ከሁሉም ትንሹ እድሜ ያለኝ አሰልጣኝ እኔ ነኝ ምንም ልምድ የሌለኝ እኔ ነኝ እና ያንን ማኔጅ አድርጌ ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር አብሬ ተስማምቼ ሰርቼ ውጤታማ መሆን በጣም በጣም ከባድ ጊዜ እሱ ነበር እና በጣም ደስተኛ ያደረገኝ ዓመት እሱ ነው።
ቡድንህ አንድ ከባድ ጨዋታ ካለበት የተጫዋቾች የአካል ብቃት እና የስነ-ልቦና ዝግጅት ምን ያህል ትኩረት ትሰጣለህ?
እዚህ ላይ ነው ይመስለኛል ብዙ ጊዜ እኔ ላይ ለየት የሚለው በተለይ ስነ-ልቦና ላይ እኔ ጋርም ጠርቼ አይደለም የሚተኙበት ክፍል ድረስ እየሄድኩ ነው የማወራቸው ለየብቻቸው ነው ስነ-ልቦና የሚገነባው አሁንም የሚታየው ብዙ ለውጥ ከ20 ውድድሩ ላይ ካሉ ቡድኖች የኛ ቡድናችን የተሻለ ሆኖ የመጣው በስነ-ልቦና ከልጆቹ ጋር በጣም ጥሩ ቀረቤታ አለኝ ይሄ ውጤታማ አድርጎኛል ብዬ አስባለሁ ሲል ገልጿል።
በፕሮጀክትም ሳለህ አሁን በሲዳማ ቡና ላይ ተጫዋቾች አንተን አሰልጣኛቸው ብቻ ሳይሆን «አባታችን» ይሉሃል፤ ይህ ከምን የመጣ ይመስልሃል?
እንግዲህ እንዲህ አድርጌያለሁ ማለት አልችልም የማውቀው ግን አንድ ነገር ነው ስፖርተኛ በጣም ነው የማከብረው አልንቅም ሐሳባቸውን ስህተታቸውን አላገዝፍም ችግራቸው ችግሬ ነው ለእኔ እግር ኳስ ቤተሰባዊነት ነው ወደውኝ ነው የሚጫወቱት ወድጃቸው ነው የማሰለጥናቸው ይሄ ይመስለኛል ጊዜዬንም እውቀቴንም ራሴንም ስለምሰጣቸው ይመስለኛል እኔ ግን ስራዬን ነው የሚሰራው እግዚአብሔር ይመስገን እንደዚህ በሰው ልብ እንድከበር ስላደረገኝ በማለት አሰልጣኝ አመሃ ዘውዴ ገልጿል።
ለአንድ ቡድን ጥንካሬ ነው ብለህ የምታስበው ነገር ምንድን ነው?
አንድነት መሰረታዊ ነገር ነው ሲጎድልም ሲሞላም ስታሸንፍም ስትሸነፍም አንድ መሆን አለብህ የእኛ ቡድን ወደፊትም ወደ ወደፊትም ጊዜም እግር ኳስ ላይ ካለው ሁሌም የሚጨነቀው ለአንድነት ነው አንድነት ደግሞ አብሮነት ነው አንድ መሆን ትልቁን ዋጋ ይወስዳል ብዬ አስባለው ሲል ገልጿል።
በመጨረሻም ለተከታታይ ዓመት ሻምፒዮን ለመሆን 90 ደቂቃ ነው የቀረህ ለዝህ ጨዋታ ምን ታስባለህ?
በአጋጣሚ ያው ከድቻ ጋር ነው የፍፃሜ ጨዋታ የሚናደርገው ከባድ ጨዋታ ነው ሶስት ጊዜ ተገናኝተናል በዚህ ዓመት ሁለቱን አሸንፈናል አንድ ተሸንፈናል በመጀመሪያ ጨዋታ ከእነሱ ጋር ነበርን 3ለ2 አሸንፈናቸዋል በጣም ተዘጋጅተው እንደሚመጡ እናውቃለን ነገር ግን እኛ ግዴታ ተከታታይ ማሳካት እንዳለብን ስለምናምን ማድረግ ያለብንን ነገር ሁሉ ሁሉንም ነገር እናደርጋለን ስል ገልጿል።
እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስህ ለሌሎች አሰልጣኞች ይጠቅማል ብለህ የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ?
በመጀመሪያ ምንም ነገር ላይ ይሁን ፈጣሪህን ማመሰገን ነው ሁሉም ሰው በሚያመልከው እምነት መንፈሳዊ ነገሩ ጠንካራ ሊሆን ይገባል ማለት የምትፀልየው ጸሎት ነው ፍሬ የሚያፈራው በተጨማሪ ያንተ ጥንካሬ መሰረታዊ ነገር ነው ስታሸንፍም ስትሸነፍም ስትወድቅም ስትነሳም ሁልጊዜ ራስህን ጥፋተኛ እያደረግክ መስራት አለብህ ስታሸንፍም «ጎበዝ ነኝ» እንደምትለው ስትሸነፍም «እኔ ነኝ ጥፋተኛው» ብለህ መውሰድ አለብህ እነዝህ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ካደረግክ ሁሉም ነገር ሰላም ይሆናል ብዬ አስባለሁ ሲል ሀሳቡን ቋጭቷል።

