ጋሞ ጨንቻ መሪነቱን ሲያጠናክር የካ ክፍለ ከተማ ነጥብ ጥሏል!

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 15ኛ ሳምንት ጅማ ስታዲየም በመጀመሪያ ቀን ሶስት ጨዋታዎች ሲያስተናግድ መሪው ጋሞ ጨንቻ ነጥቡን ወደ 34 ያደረሱበትን ድል ማስመዝገብ ችሏል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ 15ኛ ሳምንት ጨዋታ በዋና አሰልጣኝ ማቴዎስ ለማ የሚመራው ጋሞ ጨንቻ 1ለ0 ሻሸመኔ ከተማ በማሸነፍ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል።

የጋሞ ጨንቻን ግብ ታደለ ፈለቀ በፍጹም ቅጣት ምት 39ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።

ጋሞ ጨንቻ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ
10 ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ
በ1 ጨዋታ ሽንፈት አስተናግዶ
4 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ 34 ነጥቦችን በመሰብሰብ 1ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ቃሲም የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ በበኩሉ በ21 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ወደ 2019 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከሚደረገው ፉክክር ውስጥ መውጣቱንም አረጋግጧል።

7:30 በተካሄደው ጨዋታዎች ሐረር ከተማ 3ለ1 ነቀምቴ ከተማን በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ 2ኛ ድሉን በማስመዝገብ ከወራጅ ቀጠናው በግብ ክፍያ አቃቂ ቃሊቲን በመብለጥ በ10 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ዋና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቻው (ማንጎን) ያገደው ሐረር ከተማ በም/አሰልጣኝ መሣይ በየነ እየተመራ በጅማ ከተማ የመጀመሪያ 3 ነጥብ ማሳካት ችሏል።

ለሐረር ከተማ የማሸነፊያ ግቦችን
ተስፈኛው ታዳጊ አብዱልፈታ ሙህዲን ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንዷን ግብ አብርሃም አሰፋ ማስቆጠር ችሏል።

ነቀምቴ ከተማን ከሽንፈት ያልታደገችውን ጎል ታፈሰ ሠርካ ማስቆጠር ችሏል።

ነቀምቴ ከተማ በውድድር ዓመቱ 15 ያህል ጨዋታዎችን አድርጎ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም።

10:00 ሰዓት ላይ በተደረገው ጨዋታ
የካ ክ/ከተማ 1ለ1 ከአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ አቻ ተለይቷል።

ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪው ድልነሳው ሽታው የውድድር አመት 7ኛ ጎል ማስቆጠር የቻለ ሲሆን 82ኛ ደቂቃ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፈድሉ ድሌ አስቆጥሯል።

ዋና አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን ያሰናበተው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ጨዋታው በአቻ ውጤት ማጠናቀቁን ተከትሎ ነጥቡን 10 በማድረስ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የአሰልጣኝ ያሬድ ቶለራ (ድሬ) ቡድን የካ ክ/ከተማ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁን ተከትሎ ከመሪው ጋሞ ጨንቻ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ሰፍቷል።

ዛሬ የሚካሄዱ ጨዋታዎች

7:30   ንብ ከ ቡራዩ ክ/ከተማ
10:00 ባቱ ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና ይጫወታሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *