ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካሄድ ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 16ኛ ሳምንት በጂማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆነ ቀን 7:30 በተከናወነው ጨዋታ መሪው ጋሞ ጨንቻ ከ ሐረር ከተማ ጋር ያደረጉት ሲሆን ግብ ሳይቆጠር 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በዋና አሰልጣኝ ማቴዎስ ለማ የሚመራው ጋሞ ጨንቻ 16 ጨዋታዎችን አድርጎ ነጥቡን ተከታዮቹ ባቱ ከተማ እና የካ ክ/ከተማ ከመጫወቱ በፊት ወደ 35 ከፍ ማድረግ ችሏል።

በአሰልጣኝ መሳይ በየነ የሚመራው ሐረር ከተማ ላለመውረድ በሚያደርገው ብርቱ ፉክክር ከመሪው ጋሞ ጨንቻ አንድ ነጥብ በማሳካት 16 ጨዋታ አድርጎ 11 ነጥቦችን በመሰብሰብ 9ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ቀን 10:00 ሰዓት ላይ በተካሄደው የ16ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ከሻሸመኔ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በውድድር ዓመት 3ኛ ድሉን ያስመዘገበው አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በውጤት ማጣት ምክንያት ከዋና አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ጋር በስምምነት ከተለያዬ በኋላ በምክትል አሰልጣም እየተመራ ብቆይም በዛሬው ጨዋታ በ5 ቢጫ ምክንያት በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ያዕቆብ ፍሰሃ እየተማራ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።
በብርሃኑ ቃሲም የሚመራው የሻሸመኔ ከተማ 15ኛ ሳምንት ጨዋታውን በየካ ክፍለ ከተማ 1ለ0 ተሸንፎ የተመለሰ ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ 21ኛ ደቂቃ መሐመድ ኑረዲን ከቅጣት ምት የተመለሰውን ኳስ ሁለት ተጨዋቾችን ቀንሶ ለዘካሪያስ ፍቅሬ የሰጠውን ኳስ ዘካሪያስ ፍቅሬ ከመሐል ሜዳ አከባቢ ለአፍዴል መህዲ ያቀበለውን ኳስ በአንድ ንክኪ ግብ ጠባቂውን ሄኖክ አስጨናቂ ሽውዶ በማለፍ ሻሸመኔ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛ አጋማሽ 60ኛ ደቂቃ ከአቃቂ ቃሊቲ የግራ መስመር ተመላላሽ አማኑኤል ተስፋዬ ያሻማውን ኳስ ይታገሱ ምንዳ ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት የመጀመሪያ የኳስ ንክኪው የተበላሸ የሚመስል አጋጣሚ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ግን የግብ ጠባቂው በርሱፍቃድ ተፈሪ ስህተት ታክሎ ይታገሱ ምንዳ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ ማስቆጠር ችሏል።
የመጀመሪያ ግብ ከተቆጠረ በኋላ 62ኛ ደቂቃ የቅጣት ምት ያገኙት አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማዎች ሳምሶን ተሾመ ቀጥታ ወደ ጎል የመታው ኳስ የጎሉን አግዳሚ ብረት ገጭቶ ሲመለስ አጥቂው ቴዎድሮስ አበራ አግኝቶ ጎል በማስቆጠር አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ከጨዋታውን ሶስት ነጥብ ይዞ እንድወጣ ማድረግ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ13 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሻሸመኔ ከተማ በ21 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ይገኛል ።
የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን
4:00 ሰዓት’
ነቀምት ከተማ ከ ቡራዩ ክ/ከተማ
7:30 ሰዓት’
የካ ክ/ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና
10:00 ሰዓት’
ባቱ ከተማ ከንብ የሚጫወቱ ይሆናል

