ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረጉ ተጨዋቾች ለሸገር ከተማ ፈረሙ

ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ከ22 ዓመት በኋላ እንድታልፍ ትልቅ አስተዋፆ የነበራቸው ሦስት ተጫዋቾች በይፋ ለሸገር ከተማ ፈርመዋል።

በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ዳዊት ካሳው ፣ አምበሉ ቢንያም አብርሃ እና በስነ ስርዓቱ ላይ ያልተገኘው ግብ ጠባቂው ተመስገን ከበደ ናቸው ፊርማቸውን ያኖሩት።

ተጫዋቾቹ በስሪ ፖይንት አካዳሚ የጎለበቱ ናቸው። በዛሬው የፊርማ ስነ ስርዓትም የአካዳሚው ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በሸገር ከተማ በኩልም የክለቡ ፕሬዚዳንት ተወካይ ተገኝተው ተጫዋቾችን ለማስፈረም የፈለጉበትን ምክንያት አብራርተዋል።

ሸገር ከተማ ባለቤትነታቸው ስሪ ፖይንት ከሆኑት ሦስት ተጫዋቾች ውጪ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሰለጠነው ዘላለም መንግስቱንም አስፈርመዋል።

ሸገር ከተማ ለስሪ ፖይንት አካዳሚ ለእያንዳንዱ ተጫዋች 500 ሺ ብር ለመክፈል ተስማምቷል።

ተጫዋቾቹም በወር 50 ሺ ብር የሚያስገኝላቸው የሦስት ዓመት ውል ተፈራርመዋል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀው ሌሎች ክለቦች ከአካዳሚ ወይም ከፕሮጀክት ተጫዋች ሲወስዱ በዚህ መልክ ማካካሻ ከፍለው መሆን እንዳለበት ለማሳየት ነው ብለዋል።

ተጫዋቾቹ በቀጣይ የውጪ እድል ካገኙ ክለቡ ለመተባበር ዝግጁ ነው ተብሏል።

በተሻለ ገንዘብ ዝውውር የሚፈፅሙ ከሆነ ደግሞ ለስሪ ፖይንት እዚህ ላደረሰበት የማካካሻ ገንዘብ እንደሚኖረው ተነግሯል።

ይህ ሂደት ታዳጊዎችን ለማፍራት ለሚጥሩ አሰልጣኞች ፣ ፖሮጀክቶች እና አካዳሚዎች ትልቅ ተነሳሽነት እንደሚፈጥር አቶ ባህሩ ጥላሁን በማጠቃለያ ንግግራቸው ላይ ጠቁመዋል።